የአጼ ምኒልክ ዘመናዊ ጥበብን መውደድና ወደ ሀገራቸው ለማስገባት የሚያረጉትን ጥረት በእንግሊዝ ሀገር ሆኖ
ይሰማ የነበረው /Bentley/ ቤንትሌይ ምኒልክ ታሪኩን ሰምተው ለማየት እጅግ የጓጉለትን መኪና ለምን
አልወስድላቸውም ብሎ ተነሳ: ሃሳቡንም "ዌል ሲልይ ቱል ኤንድ ሞተር ማኒፋክቸሪን" /well sell toll and
motors manufacturers/ ለተባለ ድርጅት አቅርቦ ከድርጅቱ ጠንካራ መኪናን አገኘ ከዚህም በኋላ
/Bentley/ ቤንትሌይ ከጓደኛው ዌልስ ጋር በመሆን መኪናዋን ይዘው ጉዞ ወደ ኢትዮዽያ ጀመሩ ከ27 ቀን የባህር
ጉዞ በኋላ ጅቡቲ ደረሱ ከጅቡቲም ድሬደዋ ገቡ: በድሬደዋና በሐረርም ጥቂት ቀናትን ቆይተው ከዚያ ጉዞዋቸውን ወደ
አዲስ አበባ አደረጉ: አሸዋማ ቦታዎች ላይ ሰዎች ድንጋይ እያነጠፉ መንገዷን እያቀኑ: አንዳንዴም በበቅሎ እየተጐተተች:
ድንጋያማ ቦታና ወንዝ ሲያጋጥም ደግሞ በሰው ሸክም እየተሻገረች: ተራራ ሲሆን እየተገፋች ታኀሳስ 20 ቀን 1900
ዓ/ም የመጀመሪያዋ መኪና አዲስ አበባ ደረሰች: ታኅሳስ 22 ቀን 1900ዓ/ም አጼ ምኒልክ ከእንግሊዝ ሀገር
የመጣችሁን መኪና ሊመለከቱ ወጡ መኪናዋን ይዟት የመጣው /Bentley/ ቤንትሌይም የሚገባውን ገለፃ ሰጠ ምኒልክም
እየተዟዟሩ ዝቅ ከፍ እያሉ መኪናዋን በሚገባ ተመልክተው ፍጥነቷንም ለማወቅ «አየህ /Bentley/ ቤንትሌይ እኛ
በበቅሎ ከዚህ ገበያ ደርሶ መልስ ግማሽ ሰዓት ይበቃናል የመኪናዋን ፍጥነት ማወቅ እንድችል ገበያው ዳር የሚሸጥ
አትክልት አለና ሄደህ በመኪናህ እሱን ይዘህ ና?» አሉት: ፈረንጅ ተንኮለኛ ነውና እንዳያሞኙኝም ብለው አብረው
ሁለት መኳንንቶቻቸውን ላኩ ቤንትሌይም ከነመኳንንቱ የተላከው ቦታ በፍጥነት ደርሶ መጣ ምኒልክም ሰዓታቸውን አይተው
«ጥሩ ነው 6 ደቂቃ ሆናችሁ» አሉ: ከዚያም ምኒልክ መኪናዋ ላይ ወጥተው ከነጂው ጐን ተቀመጡ መኪናዋም ከቀስታ
ፍጥነት ተጀምሮ እስከ መጨረሻ ፍጥነት ድረስ እየተነዳች የአዲስ ዓለምን መንገድ አስር ማይል ሄደው ተመለሱ: ከዚህም
ቀን በኋላ አጼ ምኒልክ መኪናዋን መንዳት ተለማምደው ለፈተና ቀርበው ሁለት ሰዓት ሙሉ በሚገባ በመንዳት ችሎታቸውን
አሳዩ:: ሄልም በመጽሐፉ ''ፐርፌክት ድራይቨር'' /Perfect Driver/ ብሏቸዋል ::በምስሉ ላይ
የምንመለከታት መኪናም በምኒልክ ዘመን ከገቡ አምስት መኪናዎች መካከል አንዷ ስትሆን በአሁኑ ሰዓት በብሔራዊ ሙዚየም
ግቢ ውስጥ ትገኛለች:: ይች መኪና ዘንድሮ 108 ዓም ሞላት! መኪናዋ ወደ ሃገር ስትገባም በግራና በቀኝ
የኢትዮዽያ እና የእንግሊዝን ባንዲራ አንጠልጥለውባት ነበር::
ትልቅ ራዕይ የነበራቸው የቀደሙት አባቶቻችንን እናከበራለን እናፈቅራለን::